ፀሐይ ኢንደስትሪ አ.ማ. 13ኛ መደበኛ ጉባኤ ታህሳስ 12 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሆቴል ተካሂዷል። በስብሰባው ላይ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ፈንታ ንግግራቸውን የጀመሩት ጥሪውን አክብረው በስብሰባው ላይ የተገኙትን ባለአክሲዮኖች በማመስገን ነው። የፀሐይ ኢንዱስትሪ አ.ማ. የዳይሬክተሮች ቦርድ በ2016 በጀት ዓመት የታቀዱ የተለያዩ ተግባራት እንዲከናወኑ ለማህበሩ ማኔጅመንት ተገቢውን አመራርና አቅጣጫ የመስጠት፣ የመከታተልና ተገቢውን ድጋፍ የማድረግ ተግባር ማከናወኑን ገልፀዋል።
በበጀት ዓመቱ ካለፉት ቅርብ ዓመታት በባሰ ደረጃ በሀገራችን በተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ዕጥረት የተነሣ ለፋብሪካ ምርት በቂ ጥሬ ዕቃ ለመግዛት ባለመቻሉ የማህበሩ አፈፃፀም ካቀድነው አንፃር እና ካለፈው በጀት አፈፃፀም ያነሰ ሆኗል፡፡ ሆኖም አፈፃፀሙ ከዚህ የከፋ እንዳይሆን የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትና ማኔጅመንቱ በወሰዱት የተለያዩ አማራጭ የመፍትሄ እርምጃዎች የተነሣ ከተለያዩ ምንጮች በተገኘ ውስን የውጭ ምንዛሪ አማካኝነት ተገዝቶ በቀረበ ጥሬ ዕቃ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶች ላይ በማተኮር ተመርተው እንዲሸጡ በመደረጉ እንዲሁም ከዚህ ጎን ለጎን የወጪ ቅነሳና ቁጥጥር ስራ በመከናወኑ እና በሌሎች ምንጮች በተገኘ ገቢ ጭምር በመታገዝ አክሲዮን ማኅበራችን አትራፊ ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ በዋናነት ከላይ ከፍ ብሎ በጠቀስነው በነበረው ሀገራዊ ችግር ምክንያት ባቀድነው መጠን አፈፃፀም ባይመዘገብም ማህበሩ ለተከታታይ ዓመታት ትርፋማ ሆኖ መቀጠሉ እና ሀብት እያፈራ መገኘቱ በራሱ አበረታች ስለሆነ የድርጅቱን የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላትን፣ የተከበሩ ባለአክሲዮኖቻችን፣ እንዲሁም አጋር ድርጅቶችም የሚቻላቸውን ድጋፍና እገዛ በማድረጋቸው በዚህ አጋጣሚ በራሳቸው እና በዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ስም አመስግነዋል፡፡